Wednesday, February 1, 2023

በቋንቋ መገልገልን እንደፖለቲካ መሳርያ

 

አቶ ዋስይሁን

         አቶ ዋስይሁን እና ጀሌዎቹ የፖለቲካ ስካራቸውን ለማብረድ የተጠቀሙት ስልት “ቅዳሴ በኦሮምኛ ስለማይቀደስ ሕዝቡ እምነቱን ቀየረ።” የሚል የአዛኝ ቅቤ አንጓችነትን አካኸኼድ ነበረ። በምዕራብ ወለጋ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ወንጌል ማስተማር የተጀመረው ኢሀዴግ ሀገሪቱን በተቆጣጠረበት ማግስት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ሲባል ከዚያ በፊት ሲሰጥ አልነበረም ማለት ሳይሆን ተጠናክሮ የቀጠለው ለማለት እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።
ምክንያቱም እነ ቀሲስ ገመቹ፣መጋቤ ሃይማኖት ይኄይስ ሞገስ፣ቀሲስ ዋስይሁን፣ኦርዶፋ፣ቄስ በዳሳ እና ሌሎችም በየገጠር አድባራቱ እየዞሩ ሲያስተምሩ የኖሩት በአፋን ኦሮሞ እንደሆነ እማኞች የሚመሰክሩት እውነት ነውና። የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ የማይችሉትም እያስተረጎሙ በትርጁማን ያስተምሩ እንደነበረ ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ባደረግነው ጥናት ለማረጋገጥ ችለናል።

ቤተክርስቲያን በልዩ ልዩ  ቋንቋዎች የምታስተምረው ሰዎችን ለማስደሰት ሳይሆን አምላካዊ ትእዛዝ መፈጸም ተልዕኮዋ ስለሆነ ነው።  “ካልሰሙ እንዴት ያምናሉ?ካለመኑስ እንዴት ይጸድቃሉ?” ጌታም ለቅዱሳን ሐዋርያት አባቶቻችን ከሚያውቁት አንድ ቋንቋ ተጨማሪ 71 ቋንቋዎችን የገለጸላቸው በቋንቋ ምክንያት ወንጌል ከመስፋፋት እንዳይገታ መሆኑን ጠንቅቃ ትረዳለች። በርግጥ የቀደሙት አባቶቻችን መናፍቃኑ በሠሩት መጠን ጠንክረው ሰርተዋል ለማለት ያስቸግራል።
የሆነው ሆኖ በእነ ዋስይሁን አመለካከት ክርስቲያኖችን በሃይማኖታቸው ለማጽናትም ሆነ ወደ ቀደመች እምነታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያግዘው ስብከተ ወንጌል እንጂ ቅዳሴ በኦሮምኛ መቀደሱ እንዳልሆነ መረዳት ጥናት አያሻውም። ምክንያቱም የቅዳሴን ትርጉም የማያውቀው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን ግዕዝን ያልተማረ የየትኛውም ብሔር ተወላጅ እንደሆነ እሙን ነውና። ሌላው ቅዳሴ የጸሎት አገልግሎት ነው። ሰብከተ ወንጌል የቅዳሴው አንድ አካል ሲሆን ሲሰጥ የኖረው በኦሮምኛ ቋንቋ እንደሆነ ከዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በላይ እነ ቄስ በጻሳ ህያው ምስክር ናቸው።
ትግላቸው ስለሰው ልጅ መዳን በማሰብ በፍቅርና በትህትና ሳይሆን በትዕቢትና በመናቅ ቢሆንም ብጹዕ አቡነ ሔኖክ ቅዳሴ ወደ አፋን ኦሮሞ እንዲተረጎም ለቅዱስ ሲኖዶስ አቅርበው ሲኖዶስም ያለምንም ማንገራገር ተቀብሎ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶበት ታትሞ ተሰራጭቶ በአገልግሎት ላይ እንዳለ እንኳንስና ኦርቶዶክሳውያን ሙስሊሞች እና ፕሮቴስታንቶች ይመሰክራሉ። በጣም የሚገርመው ግን በኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ትምህርታቸውም ሆነ የጸሎት ሥርአታቸውን የሚከውኑት በአረብኛ ሲሆን እነሱ ላይ የተነሳ አብዮት ግን የለም። ታዲያ በኦርቶዶክስ ላይ የበረቱት ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ግድ ይለናል።
ቅዳሴ ወደ ኦሮምኛ መተርጎሙ እነዚህን አካላት አላስደሰታቸውም። ምክንያቱም ታሪክንም የመሻማት አባዜ የተጠናወታቸው ስለሆኑ። በእነሱ ያልተወጠወጠ ወጥ ስለማይጣፍጥ! ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የቀድሞው የደቡብ ምዕራብ ሻዋ ሀ/ስብከት ጳጳስ የነበሩት ሳዊሮስ በምን ሒሳብ የቋንቋው ጠበቃ ሊሆኑ እንደቻሉ ሳስበው እጅግ በጣም ይደንቀኛል። ምክንያቱም በሀ/ስብከታቸው በሁከት ፈጣሪነታቸው የሚታወቁ፣ከክፉ ሥራቸውም የተነሳ ስጋት ስለሚያድርባቸው/ሀጢያተኛን ማንም ሳያሳድደው ሥራው ያሳድደዋል እንዲባል/ አንድ ቀን ሀገረስብከታቸው አድረው የማያውቁ፣ሀገረ ስብከቱ ላይም እዚህ ግባ የሚባል አገልግሎት ያልፈጸሙ እንደሆኑ የወሊሶ ሕዝበ ምዕመን ህያው ምስክር ነው። ይኽንን ሳስብ “መጽሐፍ ምናምንቴ ከፍከፍ ያለበት ዘመን” ያለውን ያስታውሰኛል።
ጉዳዩ በግልጽ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያለበት መሆኑን እንደነዚህ ያሉ ከእውቀት፣ከአባታዊ ሞገስና ክብር የተራቆቱ፣እግዚአብሔር ለማይረባ አዕምሮ አሳልፎ ከሰጣቸው ግለሰቦችን በመጠቀም ሴረኛው መንግስት ሰሞኑን ምዕራብ ወለጋ ላይ የሠራውን ማየት በቂ ነው። እነዚህ ሰዎች ሃይማኖተኞች አለመሆናቸውን በውል እንረዳለን። ምክንያቱም ወገኞቻችን በሃይማኖታቸው ምክንያት ሻሸመኔላይ፣ምዕራብ ሸዋ ላይ፣ሰሜን ሸዋ ላይ እና ሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች ላይ እንደበግ ሲታረዱ፣አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት እንደችቦ ሲነዱ ቃል አልተነፈሱም። ከዚያ ይልቅ ጎንደር ላይ በተፈጸመው ግድያ የሙስሎሞች ጠበቃ ሆነው ሲሞግቱ አስተውለናቸዋል። ጫካ አለ የሚሉት ኦነግም ቀኝ እጃቸው ስለሆነ በነገር ሁሉ ይደግፉታል እንጂ ምን ሲሆን ይቃወሙታል?። እንቀጥላለን።

No comments:

Post a Comment

በሲሞን መንገድ ላይ ተገኙት “አባ” ወ/ኢየሱስ ኢፋ (ፍቅሩ ኢፋ) - ክፍል ሁለት

  እኚህ ሰው የእግዚአብሔርን ጥሪ ተቀብለው መንፈሳዊ ትምህርታቸውን መጀመራቸው አያጠራጥርም። በዚህም የሕይወት ምርጫቸውንም ቅዱስ ጳውሎስ “እንደኔ ብትሆኑ እወዳለኹ” ያለውን ተከትለው በሙሉ ጊዜያቸው እግዚአብሔርን እያመሠ...