ትናነት ጥር 23 2015 ዓ/ም በሰላምና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሰጡት መግለጫ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተደረገው ሕገወጥ ድርጊት ዓላማው ምን እንደሆን በግልጽ የሚያሳይ ማብራሪያ ነው። አንዳንድ ያነሱትን ሃሳቦች አሁን መንግስትዎ እያደረገ ካለው ድርጊት ጋር አያይዞ መገምገም የማብራሪያውን ዓላማ ለማወቅ ይረዳል።
1. ፀረ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትርክት ላይ የተመሠረተ እና ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።
1.1.
ጠቅላይ ሚንስትሩ በንግግራቸው ከቤተ
ክርስቲያኒቱ ሕግ ውጭ የተፈጸመውን የጳጳሳት ሹመት ፈጻሚዎቹ እንዳሉት በኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መሠረት የተደረገ ነው ሲሉ የዓላማ መስማማት
እንዳላቸው ከማሳየትም በላይ፣ ድርጊቱን ሕጋዊ ለማስመሰል ሞክረዋል፡፡
1.2. በተለያዩ የቀድሞ መንግስታት ጳጳሳት እና በተለይም
ፓትርያርኮች በነገሥታቱ፣ በኋላም ከዛ በኃላ በተነሱ መንግስታት ምርጫ እና ሹመት ይሾሙ እንደነበር በመጥቀስ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ
ምንም ዓይነት የሹመት ሥርዓት እንዳልነበራት፣ እንደውም ከዚህ በፊት የታየውን የመንግስታት ጣልቃ ገብነት አጽድቀው፣ የቅ/ሲኖዶሱን
ምላሽ ከብሔር ፖለቲካ ጋር ለማያያዝ መሞከራቸው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሁሉ እንዳልሆነች የሚነሳውን የሐሰት ትርክት የሚያጠናክር ነው፡፡
1.3. በትግራይ ያሉ አባቶች በራሳቸው ቋንቋ እየተገለገሉ ከቤተ ክርስቲያን ወጥተናል ሲሉ ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ፣ በኦሮሞ
ለሚነሳ ጥያቄ ይሄ ሁሉ ግርግር በማለት፣ ጉዳዩ በተለየ ሁኔታ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ምንም ምላሽ ላለመስጠት የተደረገ አስመስለው
አቅርበዋል፡፡
1.4. ክቡር ጠቅላይ ሚነስትር ለሁለት ሺህ ዓመታት ሕዝቡን በቁንቋ እና በዘር ሳትከፋፍል አጣምራ የኖረች ቤተ ክርስቲያንን የዘር ፖለቲካ ለወለደው ችግር ምክንያት አድርጎ ማቅረብ ቤተ ክርሲትያኗን ለማጥፋት የሃሰት ትርክት ከሚያስተጋቡ አካላት ተልይቶ አይታይም። ይልቅስ አሁን በቤተ ክርስቲያን የተፈጠረው ችግር መንግስት ለሚመራው ዘር ተኮር ፖለቲካ የውድቀት ማሳየ መሆኑን ነው የሚያስገነዝበው። ቢያንስ መንግስት የእምነት ተቋማትን ከዚህ ለመጠበቅ ተገቢውን አስተዋጽኦ ማድረግ ሲገባው በአንጻሩ በዚሀ ጥቂት ቀናት ውስጥ እንደሚታየው የጠቅላይ ሚንስትሩ መንግስት የችግሩ ፈጣሪ እና መሪ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
2. መረጃዎችን በተሳሳተ መልክ በማቅረብ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ
1.1.
ከዚህ በፊት የነበረውን የቤተክርስቲያን
አባቶች ልዩነትን ለማጥበብ ያደረጉትን ውለታ ጠቅሰው በሚያብራሩበት ክፍል፣ በውጭ የነበሩ አዳዲስ ጳጳሳት ከጵጵስና በፊት ባለው
መዓረግ እንኪደርሱ በቤተ ክርስቲያን የነበሩ በመሆናቸው በእርቁ ከነባሮቹ ጋር አብረው የሲኖዶስ አባል እንዲሆኑ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
ልዩነቱን በትንሹ ለማንሳት ግን፣ የውጪ አገሩ ሲመት የተፈጸመው በፓትርያርኩ በበጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ መሪነት እንጂ ራሱን
ፓትርያርክ አድርጎ በሾመ ሕገወጥ አካል አይደለም።
1.2. “አሿሿም ላይ አድሎ አለ፣ ህገመንግስታዊ መብታችን አልተጠበቀም የሚሉ ጥያቄች መጡ፣ መከርን አልተደመጥንም፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ
በቋንቋ ልማር ሲል አይ አያስፈልግህም ልንል አልችልም” በማለት ቤተክርስቲያኒቱ በኦሮምኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች አገልግሎት እየሰጠች
እንዳልሆነ እና ይህንኑ አገልግሎት ለማሳደግ እንዳልተዘጋጀች በማስመሰል ለማብራራት ሞክረዋል፡፡ ሁለቱ ክስተቶች በምንም የማይገናኙ
መሆናቸው ግልጽ በሆነበት ሁኔታ ሆን ብሎ የተሳሳተ መረጃን በመስጠት፣ በተለይም በኦሮሞ ተወላጆች የቀረበ ጥያቄ ሲሆን የተለየ ምልሽ
እንደተሰጠው በማስመሰል የብሔር መልክ ለመስጠት እና ቤት ክርስቲያኗን ለመውቀስ ሞክረዋል፡፡
1.3. ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ወጥ ሢመት የፈጸሙትን እና የተሳተፉትን አካላት ማውገዙን ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር ሳይሆን ሌላ
መልክ ለማስያዝ ሌላው ያነሱት ሃሳብ፣ በሰሜኑ ክፍል ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ ያሉ ጳጳሳት ከቤተ ክርስቲያን ተለይተናል ሲሉ ቅዱስ
ሲኖዶስም ሆነ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አካላት ምንም ነገር እንዳልተናገሩ ገልጸዋል። ነገሩ “It is like
comparing apples and oranges.” እንደሚባለው የፈረንጆች ብሂል
ነው። ምክንያቱም፡
2.1.1. “ተለይትናል” አሉ እንጂ ፓትርያርክም፣ ጳጳሳትም አልሾሙም። የኑፋቄ ትምህርት ካልሆነ ቤተ ክርስቲያን ሰውን በሕገወጥ ድርጊት
እንጂ በንግግር ምክንያት ብቻ አታወግዝም።
2.1.2. በጦርነቱ በትግራይ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመው እልቂት ገና ተነግሮ አላለቅም። በብሶት የተነገረን እና የተፈጸመን ተግባር
የመከፋፈል ዓላማ ይዘው ከተነሱ ሐሰተኞች ጋር ማወዳደር አገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ገና አልተረዱትም ያሰኛል።
2.1.3. በሰሜኑ ያሉ አባቶች ‘ተለይተናል’ ሊሉ የሚችሉበት ፖለቲካዊ ጫና ሊኖር እንደሚችል እየታወቀ እና ችግሩ ከሰላም መስፈን
ጋር በራሱ እንዲሚፈታ እየታወቀ ‘ነጻነት’ ባለበት አገር ሕገ ወጥ፣ ሕዝብን እና አገርን የሚከፋፍል ተግባር ከፈጸሙ አካላት ጋር
ማወዳደር ተገቢ አይደለም።
2.2. ከዚሁ ጋር አያይዘው ይህ መንግስት ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከአባቶች እርቀ ሰላም ጀምሮ የተለየ ድጋፍ ሲያደርገ መቆየቱነ ገልጸዋል። ለዚህም አንዱ ማሳያ ያደረጉት መንግስታቸው በአዲስ አበባ መስተዳድር ካሏት ይዞታዎች ለተወሰኑቱ ብቻ ያደረገውን ሕጋዊ ይዞታ የማረጋገጥ ተግባር፣ ለሌሎች የእምነት ተቋማት ከተደረገው አዳዲስ የመሬት ስጦታ ጋር በማነጻጸር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች የእምነት ተቋማት በበለጠ ሰፊ የመሬት ሥጦታ እንዳገኘች አድርገው ማቅረባቸው ነው፡፡ ይህ መረጃ ትክክል ቢሆን እንኳ፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ያለውን የቤተ ክርስቲያኗን የመሬት ይዞታ መንጠቅ፣ የኦርቶዶክሳውያንን መፈናቀል እና መገደል ሳያነሱ ማለፍ እውነት የሚመስል የሃሰት ትርክት ማናፈስ ነው።
3. ህጋዊ ሰውነት ያላትን የሃይማኖት ተቋም
ከሕጓ ውጭ ራሳቸውን የሾሙ አካላት ጋር በእኩል ማስቀመጥ
3.1. ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ሕጋዊ የሆነውን
የቤተ ክርስቲያኗን ቅዱስ ሲኖዶስ እና በሕገ ወጥ መልኩ የተሿሿሙትን ግለሰቦች/ቡድን እንደ እኩል ሕጋዊ አካላት ሲያወዳድሩ ይሰማሉ።
ይህም፡
3.1.1. ሕጋዊ ለሆኑ ነባር ተቋማት ሕጋዊ መሠረትን
የናደ ነው፣
3.1.2. ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ ሕገ ወጥ አካል ጋር
እንዲደራደር ጫና ለማሳደር የጠቅላይ ሚንስትሩ መንግስት እየሄደበት ላለው ግልጽ የጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴ ማሳያ ነው።
3.1.3. ዛሬ ሁለቱም ችግራቸውን በድርድር የሚለው
መንደርደሪያ፣ ይሄው ሕገ ወጥ ቡድን በቀጣይም በየአህጉረ ስብከቱ የሚያከናውናቸውን ሕገ ወጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አደረጃጀቶች ዘረፋ
እና ወረራ፣ “ሁለቱም አካላት” ተስማምተው ይፍቱት በሚል ሕጋዊ የሆነ ምላሽ ከመስጠት እንዲቆጠቡ ለማመቻቸት ነው፡፡
3.1.4. እንደውም ድርድሩ ሕገ ወጥ ቡድኑ ያደረገውን ሥርዓት አልባ ሹመት ቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲቀበል በሚመስል መልኩ ቀደም ብሎ በነበረው የአባቶች እርቀ ሰላም በውጪ የተሾሙትን ጳጳሳት ቅዱስ ሲኖዶስ እንደተቀበለ አንስተዋል። ነገሩ እንደተባለው“It is like comparing apples and oranges.” ነው።
4. ፍትህ እና ሕጋዊ ከለላ መንፈግ፣ እና ወደፊትም ለዚህ እንዳልተዘጋጁ የሚያመለክት ንግግር ነው።
4.1. እንደተለመደው አገር ውስጥ ለሚፈጠር
ችግር በሙሉ መንግስት ምንም ዓይነት ተጥያቂነት እንደሌለው በተለመደ መልኩ ገልጸዋል፡፡ ራስን መግምገምና ስህተቶችን ማመን ችግርን
ለመፍታት ፍላጎት ካለው መንግስታዊ ተቋም የሚጠበቅ ነው።
4.2. ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘በሁለቱ አካላት’ መሃል
ጣልቃ እንደማይገባ አስረግጠው ተናገረዋል። ነገር ግን በመግለጫቸው ያነሷቸው ሃሳቦች በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መልኩ የተሿሿሙትን አካላት
እንደምክንያት ከሚያቀርቧቸው ጉዳዮች እና ትርክቶች ጋር የተስማማ መሆኑ በራሱ መንግስታቸው ያለውን ተሳትፎ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
ይህ ከእውነት የራቀ፣ ዓይን ያወጣ እና የሚያስገምት ሐሰት ነው። ለቤተ ክህነት የነበረውን ጥበቃ ያነሳ፣ ጳጳሳትን ጨምሮ እያንገላታ
እና እያሠረ ያለው፣ የቤተ ክርስቲያኗን ንብረት የሚያሰብረው ማነው? ሌላ የማናውቀው መንግስት አለ እንዴ? የሚያሰኝ ነው፡፡
4.3. ጉዳዩ ግን ከላይ እንደተመለከትነው፣ ይሄው
ሕገ ወጥ ቡድን በየክልል መንግስታት ጥበቃ እና ድጋፍ በቀጣይም በየአህጉረ ስብከቱ ከአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ጀምሮ፣ ወረዳ ቤተ
ክህነት እስከ አህጉረ ስብከት ድረስ ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቷን አደረጃጀቶች ሁሉ እንደፈለጉ፣ በጉልበት የመውሰድ ተግባር፣ ከለላ ለመስጠት እና ቤተክርስቲያኒቱ ለምታነሳው የፍትህ ጥያቄ “ሁሉቱም ተስማምተው
ይፍቱት በሚል ኢ_ፍትሃዊ አካሄድ ለማለፍ እንዲያስችላቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
4.4. ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ አባቶች እና የቤተ
ክርስቲያን አካላት መንግስት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እያሉ የሚማጸኑት እኮ ሀገሪቱ ፍትሐዊ መንግስት አላት ብለው ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እስኪ ወደ አገረ ስብከታቸው
እንዳይገቡ እና በምእመናን ገንዘብ በጅማ ያስገነቡትን ቤተ ክርስቲያን እንዳይመርቁ የተከለከሉተን፣ ከጂማ ኤርፖርት ታስረው ወደ
አዲስ አበባ እንዲመለሱ የተገደዱትን አረጋዊውን አባት በፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ይጠይቁ።
5. ስለፍትህ የሚደረገን የኦርቶዶክሳዊያንን እንቅስቃሴ
ሁሉ ከሰላም ማናጋት እና ብሎም መንግስትን በኃይል እስከመገልበጥ የሚቆጠር እንደሆነ መግለጻቸው፣
5.1. ይህን ችግር አስመልቶ ኦርቶዶክሳውያን፣
በዘር እና ቋንቋ ሳይለዩ ከሁሉም አቅጣጫ እያሰሙ ያሉትን ድምጽ ለመንግስት ለውጥ የሚደረግ እነቅስቃሴ ለማስመሰል እና እንዲህ ዓይነት
እንቅስቃሴን የሚቆጣጠር አቅም እንዳላቸው በማስፈራሪያ መልክ ተናግረዋል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ “ሺ ዓመት ንገሱ፣ እጅዎን ግን
ከቤተ ክርስቲያን ያንሱ” ነው የቤተ ክርስቲያን፣ የአባቶች እና የምእመናን ድምጽ።
5.2. አባቶች እና የቤተ ክርስቲያ አካላት የመንግስት ጣልቃ ገብነት አገሪቱን ወዳልተፈለገ ቀውስ ሊያደርሳት ይቻላል የሚል ሥጋታቸውን
የሚገልጹት፣ አሁን እንደምናየው መንግስት የምእመናን ድምጽ ለማፈን
እና ፍላጎቱን ለማስፈጸም ኃይል እንደሚጠቀም በመገንዘብ ነው። ነገር ግን መስዋዕትነት ቢያስከፍልም በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ
ያለው በደል በዝምታ የሚታለፍ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ለዚህ ነው ምእመናነ በየቦታው “የምንሞትለት ሃይማኖት እንጂ የምንሞትለት
ብሔር የለንም” የሚል መፈክር ይዘው የሚታዩት። ለምዕመናን ድምጽ መንግስት ጠመንጃ ሳይሆን ጆሮውን ከሰጠ ችግሮቹን መፍታት ክቡር
ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት ‘ቀላል’ ባይሆንም የሰላም መንገድ ከፋች ነው።
6. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት
ቀላል እንደሆነ መናገራቸው
6.1. አገሪቱን አሁን ላለችበት ቀውስ ከዳረጉ ነገሮች አንዱ ግዙፍ
ችግሮችን እንደ ኢምንት ከመቁጠር የመነጨ ነው። ሕዝቡን በሃይማኖት እና በማኅበራዊ ኑሮ አዛምዳ ያኖረችን ቤተ ክርስቲያን በዘር
እና በቋንቁ ለመክፈል የሚደረግን ድርጊት ‘ቀላል’ ነው ብሎ ማለፍ ወይ ችግሩን አለመረዳት ወይም ችግሩ እንዲፈታ ያለውን የፍላጎት
ማነስ ያመለክታል። ወይም የመንግስትን በችግሩ ያለውን ቀጥተኛ ተሳትፎ እና ለሕገ ወጥ አካላት የሚሰጠውን ድጋፍ ለመሸፈን የሚደረግ
ሙከራ ነው።
7. በተለያዩ የእምነት ተቋማት ለሚፈጠር ችግር የተቋማቱ ብቸኛ ችግር አድርጎ የመንግስትን ጣልቃገብነት መካድ
7.1. የእምነት ተቋማት ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ክፖለቲካ፣ ከሌብነት እና ከዘር ነጻ መሆን እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ጥሩ ምክር ነው። መንግስት እጁን ከቤተ ክርስቲያን ላይ ካነሳ ሁሉም ችግር ይቀረፋል። ሦስቱንም ችግሮ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያየ
ዘማናት ያስገባወ መንግስት ነው። የቀድሞዎቹ ስላለፈ አሁን የጠቅላይ ሚንስትሩን መንግስት ሚና ማሳያው
7.1.1. በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚደገፉ አንዳንድ የብልጽና ፓስተሮች ቤተ ክርስቲያኗን የኋላ ቀርነት ምክንያት አድርገው ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ
እና ፖለቲካዊ ቀውስ ተጠያቂ እንደሆነች ሲናገሩ በዝምታ ማለፍ
7.1.2. የቤተ ክርስቲያኗን ሕጋዊ ኅልውና ከኅገወጥ አካል ጋር አስተካክሎ ማየት
7.1.3. ቀደም ብሎ እንደተገለጸው በፖለቲካው መስመር ቤተ ክርስቲያንን በዘር ለመከፋፈል የሚሞክሩ ሕገ ወጥ አካላትን በግልጽ መደገፍ
7.1.4. ዛሬ ባደረጉት ንግግር ጭምር ቤተ ክርስቲያን የሰዎችን በቋንቋቸው የመማር መብት እንደምትገፍ የሚያስመስል ጠባ አጫሪ ንግግር
ማድረግ ናቸው።
ማጠቃለያ
የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር
በጥቅሉ ችግር ፈቺ ሳይሆን አሁን በተፈጠረው ችግር ላይ ቤንዚን ያርከፈከፈ እና ከተጠያቂነት የማያድን ንግግር ነው። ለችግሩ ሰላማዊ
መፍትሔ እንዲመጣ መንግስት ጣልቃ ገብነቱን ትቶ
1.
የቅድስ ቤተ ክርስቲያኗን ሕጋዊ ኅልውና
ተቀብሎ ሕጋዊ መብቷን ማስከበር
2. በቤተ ክርስቲያኗ እና በአገልጋዮች ላይ የሚደርሰውን መዋቅራዊ ጥቃት ማስቆም
3. የዜጎችን ሕገ መንግስታዊ ሃስብን በነጻነት የመግለጽ መብት ማክበር እና ለሚያነሱት ጥያቆ ጆሮ መስጠት አገር ከሚመራ መንግስት
እና መሪ የሚጠበቅ ተግባር ነው።
No comments:
Post a Comment