አቶ ዋሲሁን አመኑ ቤተክርስቲያንን ለመክፈል ሀገርን ለማፍረስ እንቅልፍ አጥቶ የሚሠራ ግለሰብ ነው። ይህንን ሰው ከመጥላት ሳይሆን በተጨባጭ ከሚሠራቸው ሥራዎች በግልጥ የሚታወቅ እውነት ስለሆነ ነው። ነጆ የግብርና ኮሌጅ መምህር በነበረበት ጊዜ ዲ/ን ዳንኤል የተረጎመውን የኦሮምኛ ቅዳሴ ትርጉም ከምትኩ ተኮላ ጋር ቀምተው አሳትመው ካሰራጩት በኋላ ዲ/ን ዳንኤል በድርጊታቸው ማዘኑን ስለተረዱ የኦሮሚያ ቤተክህነት እንመሰርታለን ብለው በአዲስ መልክ መንቀሳቀስ በጀመሩ ሰሞን ነጆ ላይ ባካኼዱት ጉባኤ የማስመሰል ሽልማት እንደሰጡት ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው።
ይኼንንም ለማድረግ የደፈሩት ከኛ ወገን መንግስት ተሹሟል፣ጊዜው የኛነው በሚል መንፈስ ነው። እውነትም ጊዜው/ተራው የእነሱ መሆኑን የምዕራብ ወለጋን ሀ/ስብከት መንበረ ጵጵስና በመንግስት ታጣቂ ሓይሎች ታግዘው ከክህነት የተሻሩ የሐሰት ሹመኛ ጳጳስ ተብየዎችን ሰብረው እንዲገቡ በማድረግ አረጋግጠውልናል።
ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ለመረዳት እንደቻልነው የሀሳቡ ጠንሳሽ እና ባገኘው ምቹ አጋጣሚ ሁሉ የኦሮሚያ ቤተክህነትን በማቀንቀን የታወቀው ይኼው ግለሰብ እንደሆነ ለማረጋገጥ ተችሏል። ብጹዕ አቡነ ሔኖክ ጵጵስና ተሹመው ወደ ምዕራብ ወለጋ ሲመጡ ይህ ግለሰብ የተቀበላቸው በሃይማኖት አባትነታቸው ሳይሆን በዘር ኦሮሞ መሆናቸውን ታሳቢ አድርጎ ነበር። ብጹዕ አቡነ ሔኖክ ገና ከህጻንነት እድሜያቸው ጀምረው ቤተክርስቲያን ውስጥ ያደጉ፣ንጽህና ቅድስናቸውን ጠብቀው የኖሩ፣ዓለምንና ዓለማዊነትን የተጠየፉ፣ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው እግዚአብሔርን ለማገልገል የቆረጡ ካህን እንኳን ዘር ጾታ የለውም ብለው በጽኑ የሚያምኑ አባት እንደሆኑ ተረድተናል።
ሆኖም ግን ይህ የጭቃ ውስጥ እሾህ የሆነው ይህ ግለሰብ ማንነታቸውን በውል ሳይረዳ “ሀገረ ስብከቱ በእቅድ መመራት አለበት” እያለ ስለሚደሰኩር እሳቸውም ሀገረ ስብከቱ እንዲያድግ፣ አሠራሩም እንዲዘምን ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ይህንን ግለሰብ አቅርበው ከኤች አይ ቪ መቆጣጠርያ ሥራው በተጨማሪ የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ አባል እንዲሆን አደረጉት። እሳቸው ይህንን ሲያደርጉ በሙያው ቤተክርስቲያንን ያገለግላል በሚል ቅን ሐሳብ እንጂ የተሰጠውን ዕድል እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ምዕመናንን የሚከፋፍል ሐጢያት በድፍረት ይሠራል ብለው ፈጽሞ አልጠረጠሩም ነበር።
ይህ ከክርስቶስ ፍቅር ይልቅ በዘረኝነት ፍቅር የተለከፈው ግለሰብ ግን የሀ/ስብከቱን ሠራተኞች በገንዘብ በመደለል ከጎኑ ካሰለፈ በኋላ ቤተክርስቲያን የምትበጠበጥበትን ስልት ነድፎ በማሰልጠን አሠማራቸው። በሱ አመለካከት “የኦርቶዶክሳውያን ቁጥር የቀነሰው ቅዳሴ በኦሮምኛ ስላልተቀደሰ ነው።” የሚል ሲሆን ይህንን የተሳሳተ መላምቱን ወደ ሕዝቡ ለማስረጽ ጥናት አጠናኹ በማለት ግኝቱን ለሀገረ ስብከቱ እና ለምዕመናን አቀረበ።
በጊዜው የምዕራብ ወለጋ፣ቄሌም ወለጋ እና የአሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሔኖክ ሐሳባቸው ከቅንነት የመነጨ መስሏቸው “እኛ አስበን መሥራት የነበረብንን እናንተ አስባችሁ በመጀመራችኹ እናመሰግናለን በርቱ ቀጥሉበት።” በማለት አባታዊ መመርያ ሰጧቸው። ይህ የልብልብ የሰጠው መሰሪ ግለሰብ የተፈጠረለትን ወርቃማ እድል ለመጠቀም ጊዜ አላባከነም። የቤተክርስቲያንን አውደ ምህረት በመጠቀም ያጠናውን ጥናት በተላላኪዎቹ በእነ ገረመው አፈወርቅ፣ ቄስ በዳሳ ቶላ ወዘተ በመጠቀም “እስከ መቼ ከሰሜን የሚመጡ ካህናት ይመሩናል? ቋንቋችን እስከመቼ ተጨቁኖ ይኖራል?” ማስባል ጀመረ።
የዋኹ ምዕመንም እውነት መስሎት ቃላቸውን በመስማት ቤተክርስቲያንም መበጥበጥ ጀመረች። “አካኼዳችሁ ልክ አይደለም ክርስቶስ የሞተው ያመነበት ሁሉ ይድን ዘንድ ነው።” ብለው የሞገቷቸውን በብሔር ኦሮሞ የሆኑ እውነተኛ አባቶችን ስም የማጥፋት ዘመቻ ከፈቱባቸው፣ ከፍ ሲልም የግምቢ ደብረ ፀሐይ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበሩትን አባት እስከማስደብደብ ደረሱ። ብጹዕነታቸውም ዓላማቸውን በውል ስለተረዱ ይኼንን ከፋፋይ ሀሳባቸውን እንዲያቆሙ ቢገስጿቸውም፣ “ሕዝቡን ከጎናችን አሰልፈናል ከእንግዲህ የሚያስቆመን ኃይል የለም።” በማለት ብጹእነታቸው ላይ ሕዝቡ እንዲያምጽ ከሀ/ስብከት እስከ ወረዳ ቤተክህነት ቀሰቀሱ።
የዋኹን ምዕመን “በቋንቋህ እንዳትማር፣ ቋንቋህ እንዳያድግ ተቃወሙን” ብለው በሐሰት ስለቀሰቀሱት እውነት መስሎት ተደነጋገረ፤ኦርቶዶክሳውያን የሆኑ የሌላ ብሔር ተወላጅ ካህናት እና ምዕመናን ስጋት ውስጥ ወደቁ። ምዕመናን ከቤተክርስቲያን ራቁ፣አስተዋጽዖቸውን ቀነሱ። ብጹዕ አቡነ ሔኖክም በቃላት የማይገለጽ መከራ ተቀበሉ።
በመጨረሻም ያደራጃቸውን ሴሎች በመጠቀም ብጹዕ አቡነ ሔኖክ ምዕራብ ወለጋ ላይ የጀመሩትን ሐዋርያዊ አገልግሎት፣አስደማሚ የሰብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብራቸውን፣የተጀመሩ የአብነት ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ፕሮጄክቶቻቸውን ከግብ ሳያደርሱ ጀሌዎቹን አሳምጾባቸው ያለፈቃዳቸው እንዲዛወሩ እና የምዕራብ ወለጋ ሀ/ስብከት እንዲፈርስ እና ዛሬ ለደረሰበት ምስቅልቅል እንዲደርስ አድርጓል። መለያየትን የሚፈጥር በራሱ ላይ ፈርዶ ሀጢያትን ያደርጋል። ስለጀሌዎቹ ማንነት እንመለስበታለን። ይቆየን።
No comments:
Post a Comment