ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካቢኔያቸው በሰላምና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ ተብሎ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ የመንግሥት ሚዲያዎች ሲተላለፍ ነበር። ማብራሪያው ግልጽ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ይህን ከመሪ የማይጠበቅ ንግግር በብሮድካስት ማስተላለፍ ለምን እንደተፈለገም ግልጽ አይደለም። ማብራሪያው ያለ መረጃና ማስረጃ የቀረበ ማስፈራሪያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩከተናገሩት መረዳት የሚቻለው የእነ ደመላሽ/አካለወልድ ሞጎር የሐሰት ሢመተ ጵጵስና በመንግሥት ውሳኔ የተፈጸመ መሆኑን ብቻ ነው። በዚህ በኩል ስለሰጡን ግልጽና እውነተኛ መረጃ ሳናመሰግን አናልፍም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቤተ ክርስቲያን አገር ናት” በማለት ለቤተ ክርስቲያን በጎ ዐሳብ እንዳላቸው በማስመሰል እንዳልተናገሩ፣ ዛሬ አገር አፍራሾች ሲነሡባት አገር ናት ያሏትን ቤተ ክርስቲያን ከመጠበቅ ይልቅ ከአፍራሾች ጎን መሰለፋቸው ቀድሞውንም ለአቅርቦተ ኦርቶዶክሳውያን ብቻ የተናገሩት መሆኑን ያስረግጣል። እንዲያውም መመሪያ እና ውሳኔ በሚመስል መልኩ ለቤተ ክርስቲያን ዐዲስ ቀኖና ለመሥራት ሲዳዳቸው ነበር። በአጠቃላይ ማብራሪያው ያለዝግጅት የተነገረ፣ በተፋልሶ የተሞላ፣ የሕገወጡ ቡድን እንቅስቃሴ መንግሥት መር መሆኑን ያረጋገጠ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ ሰውነት የሚጋፋ፣ ለቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ጥላቻና ንቀት ያጋለጠ እና እንደ አገር መሪ ሳይሆን እንደሕገወጥ ቡድኑ ቃል አቀባይ የቀረበ ነበር ማለት ይቻላል። ከዚህ አንጻር መሠረታዊ የሚባሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች ላይ ጥያቄና ትችት ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
1. መንግሥት ለቤተ ክርስቲያን ስላደረገው ድጋፍ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የተሰሙት እርሳቸውና መንግሥታቸው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያላደረጉላት ነገር እንደሌለ ነው። ሲኖዶስን እንዳስታረቁ፣ የተወረሱ ሕንፃዎችን እንደመለሱ፣ በሚሊዮን ካሬ ሜትር ይዞታ እንደሰጡ፣ ለቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዕድሳት ከፈረንሣይ መንግሥት ፈንድ እንዳገኙ፣ በአቡዳቢ ይዞታ እንዲኖራት እንዳደረጉ በድፍረት ሲናገሩ ነበር። እውነታው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም ጉዳዮች ላይ የድል አጥቢያ አርበኛ ሆነው ከመከሰታቸውና ክሬዲቱን ለመውሰድ ከመፈለጋቸው ውጪ “ከነገሥታቱ በኋላ እንደ እኔ መንግሥት በጎ ያደረገ የለም” የሚል ፉከራ ለማስተጋባት የሚያስችል አስተዋፅዖ የሌላቸው መሆኑ ነው። በተለይም በውጪ በሚኖሩት አባቶችና በቅዱስ ሲኖዶስ መካከል የተደረገውን ዕርቅ ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ እንደሚረዳው ቀድሞ የተጀመረና ልዑካንን በመላክ ብዙ የተደከመበት ጉዳይ ነበር። የዕርቅ ፍላጎቱም የአባቶች እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድካም ውጤት አለመሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀድሞ የነበረው መንግሥት እንደሚያደርገው እንቅፋት አለመሆናቸው የሚያስመሰግናቸው መሆኑ አልተካደም። ለዚህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ተገቢውን ምናልባትም ከሚገባቸው በላይ ዕውቅና ሰጥታለች።
“ደርግ ፓትርያርክ ሲገድል፣ ኢሕአዴግ ሲያሳድድ እኛ ግን መግደልም ማሳደድም ትክክል አይደለም ብለን በውጪና በውስጥ ያሉ አባቶችን በማስታረቅ አግዘናል” ብለዋል። እርቅንና የአገር አንድነትን በመሻት የተፈጸመ ከነበረ መልካም ነው። ነገር ግን “ደርግ ፓትርያርኩን የገደላቸው ለንጉሡ ቃለ መሐላ ፈጽመው የተሾሙ ስለነበሩ አብረው መሔድ ባለመቻላቸው ነው፤ ኢሕአዴግም በወቅቱ የነበሩትን ፓትርያርክ ያሳደዳቸው በደርግ የተሾሙ ስለነበሩ አብረው መሔድ ባለመቻላቸው ነው” በማለት የሰጡት ማብራሪያ የመንግሥታቱን ድርጊት ትክክለኛነት የሚያጸድቅ እንጂ የጸፈጸመውን ግፍ የሚያወግዝ አይደለም። የንግግሩ ዐውድ ችግሩ የፓትርያርኮች እንጂ የመንግሥታቱ ሆኖ አልቀረበም። የእርስዎ መንግሥትም ፓትርያርክ ከመግደልና ከማሳደድ ቤተ ክርስቲያኗን ራሷን ማሳደድ የሚል መርሕ መከተሉ ከሌሎች የከፋ ቢያደርገው እንጂ የሚሻል ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ሌሎች መንግሥታት በጅራፍ እንደገረፏችሁ እኔ ደግሞ በጊንጥ እነድፋችኋለሁ ያለ ነው የሚመስለው። ተደረጉ የተባሉት ጉዳዮችም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ታስበው የተደረጉ እንዳልሆኑ አሁን ላይ በቤተ ክረስቲያን ላይ እየተደረገ ካለው መረዳት ይቻላል። ስለሆነም በዕርቁ ጉዳይ ሊወስዱት የሚፈልጉትን ድካም አልባ ዋጋ ወስደው እንደጨረሱ ስንገልጽ በትህትና ነው።
የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያንን በተመለከተ የተናገሩት ግን አይደለም ዓለማዊ ነኝ ከሚል መንግሥት መሪ ከኦርቶዶክስ በአንጻር የተቋቋመ ከሃይማኖታዊ መንግሥት መሪ እንኳን የሚጠበቅ አይደለም። የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ከአገር አልፈው ዓለም አቀፍ ሀብቶች ናቸው። ለዚህ ቅርስ ዕድሳትና ጥገና ለማድረግ ኦርቶዶክስ ወይም ኢትዮጵያዊ መሆን አያስፈልግም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የተናገሩት ከዚህ ፈጽሞ የራቀ ነው። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41 (9) መንግሥት የባህልና የታሪክ ቅርሶችን የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጓል። ይህን ኃላፊነት ለመወጣት የሚፈጸሙ ተግባራት ሁሉ ከችሮታና ከውለታ ወይም ቤተ ክርስቲያንን ከመውደድ ሊቆጠሩ አይገባቸውም። የገዳማቱ ዕድሳት ማድረጊያ ፈንድ ማፈላለግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆን አስቀድሞ የተጀመረ ነው። የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የዕድሳት ፕሮጀክት ስምምነት በተፈረመበት ጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ አብያተ ክርስቲያኑን ለማደስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከመንግሥት በተጨማሪ ሌሎች አካላትም እንዲሳተፉ ጥሪ በማድረግ ሥራው እንደተጀመረ የሚታወቅ ነው። ያ ማለት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት መሆኑ ነው፡፡ ይህን እውነት በመጋፋት የተሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የአገር መሪነትን ሚና የረሳና የፈንድ ማፈላለግ ሥራው ፈር ቀዳጅ አስመስሎ ያቀረበ ስለሆነ ፈጽሞ አግባብነት ያለው አይደለም።
የደርግ መንግሥት አራት ኪሎ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ጉልበትና ሀብት ያፈራቻቸውን ሁለት መንትያ ሕንፃዎች ያለአግባብ ወስዶ መቆየቱ ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያን በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 398 መሠረት እንደ አንድ ሰው የምትቆጠር እንደመሆኗ ንብረት የማፍራት መብት ያላት ናት። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ትልቅ ውለታ የሚገልጹት እነዚህን ንብረትነታቸው የቤተ ክርስቲያን የሆኑ ሕንፃዎችን መመለሳቸውን ነው። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተለያዩ የሰበር መዛግብት በሰጠው አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ያለአግባብ ከአዋጅ ውጪ የተወሰዱ ቤቶችን ለሚመለከተው አካል ጥያቄ በማቅረብ ባለመብት መሆን ይቻላል። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን የራሷን ንብረት በአስተዳደራዊ መፍትሔ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ ማግኘቷ የተለየ ምስጋና የሚያሻው ጉዳይ ሳይሆን ሕጋዊ መብቷ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር መሪና የመንግሥት ባለሥልጣን መሆናቸውን እየረሱት ካልሆነ በስተቀር መንግሥት የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያትም ይህን መሰል ፍትሕን ለማስፈን ነው። ስለሆነም በሕግ የተፈቀዱ መብቶችን ማስከበርና ፍትሕ ማስፈን መንግሥታዊ ግዴታ እንጂ ግለሰባዊ እርዳታ አይደለም። እንዲህ ዐይነቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን አድርጌላችሁ መግለጫ ከዕውቀት ማነስ የሚነጭም ሊሆን ይችላል።
2. ለቤተ ክርስቲያ ስለተሰጣት የአምልኮ ስፍራ
የአምልኮ ሥፍራ አሰጣጥን በተመለከተ መንግሥት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማድላት ሰፊ ቦታ እንደተሰጣት የተገለጸበት አግባብ ፈጽሞ ሐሰት ከመሆኑም ውጪ መንግሥት አድሏዊ መሆኑን በግልጽ ያመነበት በመሆኑ ከፖለቲካ እርምት አንጻር እንኳን ተገቢነት የለውም። መረጃው በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ ተዘጋጅቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩም ያለምንም ማጣሪያ የቀረበ መሆኑ ከዚህ በፊትም በብዙ ማስረጃዎች ስለቀረበ ወደዚያ ትንተና መግባት ላያስፈልግ ይችላል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን እንጂ የማይገባትን አትጠይቅም፤ አዲስ አበባ ውስጥ ያሏት ይዞታዎችም ካላት ምእመናን አንጻር ፈጽሞ በቂ አይደሉም። ተደረገላት የተባለውም አልተደረገም እንጂ ተደርጎ ቢሆን እንኳን የሚያንስባት እንጂ የሚበዛባት አይደለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሌሎች ቤተ እምነቶች የተሰጠው ይዞታ ተደምሮ ለቤተ ክርስቲያን ከተሰጠው ይዞታ 1/3ኛ ያህል ነው ብለዋል። እስኪ እንጠይቅዎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡- ይህን የሰጡትን አንድ ሚሊዮን ካሬ ሜትር ይዞታ በማስረጃ ሊያረጋግጡልን ይችላሉ? በእውነት ተሰጥቶ ከሆነም ስትሰጡ ፍትሐዊ ነው ብላችሁ አምናችሁበት ነው? ከሆነ በምን ምክንያት ፍትሐዊ ነው አላችሁ? ፍትሐዊ ካልሆነስ ለምን ሰጣችሁ? በማብራሪያውስ ለሌሎች ቤተ እምነቶች ለእናንተ የተሰጠው ይዞታ ከኦርቶዶክስ አንጻር በጣም ትንሽ ነው በማለት ሲናገሩ ቅሬታ እንደማይፈጥርባቸው በምን መተማመኛ ተናገሩት? ሰጠነው ያሉትንስ ይዞታ ስትሰጡ በምን ማስተር ፕላን ሰጣችሁ? እርስዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሳለ የመሬት አስተዳደር ባለሙያ ሥራ ውስጥ መግባትዎስ ለምን አስፈለገ? በኦርቶዶክስ ላይ ያለዎትን ጥላቻና አድሏዊነት ለመሸፋፈን ያቀረቡት እንጂ በመንግሥትዎ ለቤተ ክርስቲያን የተደረገላት ጥቂት የተደረገባት ግን ብዙ ነው። በተጨማሪም የሌሎች እምነት ሰዎችን በቤተ ክርስቲያን ላይ ለማነሳሳትና ደጋፊ ለማሰባስበ የተደረግ ጥረት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
ክፍል ሦስት
3. ስለ ሕገወጡ እንቅስቃሴ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የመስጠታቸው ዋናው ምክንያት ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም በእነደመላሽ/አካለወልድ አማካኝነት የተፈጸመው መፈንቅለ ሲኖዶስ ነው። እነዚህ አካላት ያለ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና ፈቃድ ሃይማኖታዊ ቀኖናዊ ጥሰት በመፈጸም “ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ፈጽመናል” በማለት መግለጫ ሰጥተዋል። ሕገወጥ ድርጊታቸውን ለማጽደቅም ዲያብሎስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አራት ላይ እንደተገለጸው በጥቅስ በማስደገፍ የዋሀንን ለማደናገር ሞክረዋል። ይህ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን መፍትሔ ሊሰጥ የሚገባው በቤተ ክርስቲያን ነው። የጉዳዩ ባለቤት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን ደግሞ የተፈጸመው አድራጎት የሃይማኖትና የቀኖና ጥሰት ስለሆነ ሐሳዊ ሢመተ ጵጵስና ሿሚዎቹም ሆኑ ተሿሚዎቹ ተወግዘው ከቤተ ክርስቲያን እንዲለዩ ወስናለች። ይህን ውሳኔ በመቃወም በመንግሥት አካላት የሚሰጥ መግለጫ ሁሉ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 የተቀመጠውን የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት መርሕ መጣስና በቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ መግባት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጉዳዩን ሁለቱም ወገኖች በመደራደር እንዲፈቱ የሰጠነው ምክር ተቀባይነት አላገኘም፤ የትኛውንም ቡድን አንደግፍም፣ ሁለቱም ወገኖች አባቶቻችን ናቸው፤ በዚህ ጉዳይ ማንም እጁን እንዳያስገባ” በማለት ሕገወጥ ቡድኖችን በቤተ ክርስቲያን አንጻር በአቻ ወንበር በማስቀመጥ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ገልጸዋል። ክቡር ሆይ! “የትኛውንም ቡድን” ብለው ቤተ ክርስቲያንን ከአንድ ሕገወጥ ቡድን ጋር ማነጻጸርዎ ሳያንስ ሕጋዊ ሰውነት ያላትን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ ግዴታዎ መሆኑን መዘንጋትዎ በእጅጉ ያሳዝናል። የመንግሥት ጽንሰ ሐሳብ የተፈጠረው እያንዳንዱ ሰው ካለው የማይገደብ ነጻነት ሸርፎ ሕግና ሥርዓት አስከባሪ መኖሩን በማመን ጉልበተኞች የደካሞችን፣ ግልፍተኞች የታጋሾችን መብት እንዳይጋፉ ለማድረግ ነው። መንግሥት የተፈጠረበት ዓላማ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ነው። የያዙት ሥልጣን ለሕዝብ አገልግሎት፣ ከሕዝብ ያገኙት እንጂ የግልዎ አይደለም። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያንን የመደገፍ ሳይሆን የመጠበቅ እና ሕጋዊ መብቷን የማስከበር ግዴታ የመንግሥትዎ መሆኑን ለማስረዳት እንወዳለን። እርስዎ ፍላጎት ባይኖርዎት እንኳን “ማንም እጁን እንዳስገባ” የሚል ትእዛዝ ማስተላለፍዎ በሕግ ተጠያቂነት የሚያመጣ የጥላቻ ንግግር መሆኑን ሊረዱት በተገባ ነበር።
ምናልባት የተፈጠረውን ጉዳይ ምን እንደሆነ ለማስረዳት በቀላል ምሳሌ እንመልከት። ከሁለት ወይም ከሦስት ክልል ከመጡ የፓርላማ ተወካዮች መካከል የተወሰኑ አባላት ለብቻቸው አንድ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ያለ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕውቅናና ውሳኔ አሁን ያለው የፓርላማ ስብስብ ሁሉንም ያማከለ ስላልሆነ ከዛሬ ጀምሮ የፓርላማ አባላት የሚሆኑት እነዚህ ናቸው ብለው አወጁ። ከዚያም ከመረጧቸው ሰዎች ጋር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነን ብለው አስፈጻሚ አካላትን አዋቀሩ። በየክልሉና በየዞኑ የአስፈጻሚ አካላትን ቢሮ በመስበር እየገቡ ከዛሬ ጀምሮ መሪዎቻችሁ እኛ ነን አሉ። እርስዎ ከእነዚህ አካላት ጋር ጦርነት ይገጥማሉ ወይስ በድርድር ተቀብለው የተወካዮች ምክር ቤት እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል እንዲሆኑ ይፈቅዳሉ? በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመው ይህ ነው። ሦስት ሕገወጦች ተነሥተው በሌላቸው ሥልጣን ጳጳስ ሾመናል አሉ። እነዚያን ሕገወጥ ተሿሚዎች በየሀገረ ስብከቱ በመመደብ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር በመቆጣጠር ወረራ ፈጸሙ። ይህ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን በአገር መንግሥት አለ ብላ በማመን እየተፈጸመ ያለው ሕገወጥ ድርጊት እንዲቆም ለመንግሥት አሳወቀች። መንግሥትም ሕገወጦችን በመደገፍ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን በማንገላታትና በማሳደድ ለቤተ ክርስቲያን ጩኸት አሉታዊ ምላሽ ሰጠ። ሕገወጦችን በፓትሮል እያጀበ ወደ ሀገረ ስብከት እያስገባ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ከመንበራቸው ማሳደድ ጀመረ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገወጥ ሹመቱ እና በየሀገረ ስብከቱ እየተፈጸመ ያለው ወረራ በመንግሥት ይሁንታ የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ሌላ አማራጭ መፈለግ እንደሚገባን አሳይተውናል።
ጉዳዩን ቀላል አድርገው ያቀረቡበትም መሠረታዊ ምክንያት የታቀደበትና በመንግሥት በኩል በግድም ቢሆን ተፈጻሚ ለማድረግ እየሠራ ስለሆነ ነው። የቤተ ክርስቲያንን ጩኸት ለመስማት ማንም እጁን እንዳያስገባ ካቢኔዎችዎን ያስጠነቀቁበት መንገድ ልጆቹን የሚቆጣ አባት ይመስሉ ነበር። ሕገወጦችን ለመደገፍ እጅን አስረዝሞ፣ አገር የሠራችን ቤተ ክርስቲያን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር እጅን መሰብሰብ ምንም የሚያስከፍለው ዋጋ እንደሌለ ማሰብዎ አማካሪ አልባ መሆንዎን ወይም ሰነፍ አማካሪ እንዳለዎት ያረጋግጣል። ጌታዋን የተማመነች በግ ሆነው እንጂ እነ አካለወልድ ይህን ቀልድ በራሳቸው ሥልጣን እንደማይሞክሩት ከዚህ በፊት በነበረን ልምድ እናውቃቸዋለን። መንግሥት እጁን ብቻ ሳይሆን ሙሉ አካሉን አስገብቶ አይዟችሁ ባይ ደጀን፣ አዝማች ፊታውራሪ ሆኖ እየሠራ መሆኑን ቀድሞም ከሕገወጦች የፓትሮል እጀባ እና ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንግልት አሁንም ከንግግርዎ ተገንዝበነዋል።
ለይስሙላ እንኳን ሕገወጥ ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ ሌሎችም እንዲሁ ሲያደርጉ እንደነበር የገለጹት ዐሳብ በእርስዎ አድሮ አካለወልድ እየተናገረ እንጂ ራስዎ የተናገሩት አይመስልም። ውጪ የነበሩት አባቶች ጋር የተፈጸመውን ዕርቅ፣ በትግራይ ክልል የሚኖሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሰጡትን መግለጫ ከዚህ ሕገወጥ ድርጊት ጋር ለማመሳሰል የሔዱበት ርቀት የአንድነት ምክንያት (unifying factor) ሆና የኖረችዋን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ መንግሥትዎ ምን ያህል ቆርጦ እንደተነሣ የሚያስረዳ ነው። ሲጀመር በውጪ የተሾሙት ሊቃነ ጳጳሳት ሹመት ቀኖናዊ መሆን አለመሆን መመርመር የቤተ ክርስቲያን እንጂ የመንግሥት ሥልጣን አይደለም። አሁን ሾመናል፤ ተሹመናል የሚሉ አካላትንም ጉዳይ መርምሮ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ ርምጃ መውሰድ የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ነው። መንግሥት ቀኖናዊ ጥሰት በፈጸሙ አካላት ላይ የተላለፈውን የቤተ ክርስቲያን ውሳኔ ከማስፈጸም ውጪ የውሳኔውን አግባብነት የመመርመርም ሆነ አቻ ምሳሌ በማቅረብ ሕገወጡ ድርጊት እንዲጸና የመጠየቅ/የማግባባት ሥልጣን የለውም። ለግንዛቤ ያህል ግን ውጪ ያሉት አባቶች የተሾሙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ በፖለቲካ ጫና ተሰደው እንዲወጡ በተደረጉበት ወቅት ነው። ሹመታቸው የተፈጸመውም በቅዱስ ፓትርያርኩ ነው። በትግራይ ክልል የሚኖሩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተም አሁን እንደተፈጸመው ጳጳስ ሾመናል፤ ቅዱስ ሲኖዶስ አቋቁመናል የሚል መግለጫ ሲሰጡ አልታዩም።
ያልተካከለ ምሳሌ በመጥቀስ የሕገወጦቹን ዐሳብ ቃል በቃል ማቀንቀን የቃለ አቀባይነት ተግባር እንጂ አንድን ትልቅ ሀገር ከሚመራ መሪ አይጠበቅም። የተወገዙት ግለሰቦች “ሹመቱን ፈጽመን በእርቅ እና በድርድር አንድ እንሆናለን” በሚል ሒሳብ ያራምዱት የነበረው ዐሳብ ምንጩ ከየት እንደሆነም የሚያስረዳ ነው። ስለሆነም ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ በሌሉበት የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ሹመት የፈጸሙና ያስፈጸሙ አካላትን ቤተ ክርስቲያን በእርቅና በድርድር እንድትቀበል መምሪያ አዘል ማስፈራሪያ መስጠታቸው ፈጽሞ በማያውቁትና በማያገባቸው ጉዳይ ገብቶ መፈትፈት ስለሆነ ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል። ቤተ ክርስቲያን አውግዛ የለየቻቸውን አካላት በቀኖናዋ መሠረት በንስሐ እንጂ በድርድር ትመልስ ዘንድ ምድራዊት ተቋም አይደለችም።
4. በቋንቋ ስለመገልገል
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ የጠቀሱት መሠረታዊ ጉዳይ በቋንቋ ስለመገልገል ነው። ቤተ ክርስቲያን ያለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ አይደለም። ባለችበት ቦታ ሁሉ በሕዝቡ ቋንቋ ታስተምራለች። ቋንቋ ገደብ ሆኖባት አያውቅም። ቤተ ክርስቲያን አንዲት እንደመሆኗ መጠን ቋንቋዬ ይህ ነው ብላ አታውቅም። አገሯ በሰማይ ቋንቋዋም ሰማያዊ ነው። ለቤተ ክርስቲያን ቋንቋዎች ከአገልግሎት መሣሪያነት ያለፈ ሚና የላቸውም። ምእመናንን በሁሉም ቋንቋዎች ለማስተማር ቤተ ክርስቲያን የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ ሥልጠናዎችን በመስጠት ሰባክያንን እያፈራች እንዲሁም መጻሕፍትን በተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎምና በማስተርጎም ሁሉንም በሚሰማው ቋንቋ እያገለገለች ትገኛለች። በዚህ አንጻር ኃላፊነቷን ባትወጣ እንኳን ጠያቂዋ ሰማያዊው አምላክ እንጂ ምድራዊ ንጉሥ አይደለም። ሕዝቡ በሚሰማው ቋንቋ አገልግሎት መስጠት የቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋ ቢሆንም መንግሥት ግን በዚህ ቋንቋ ስበኩ በዚህ ቋንቋ አትስበኩ ብሎ ማዘዝ አይችልም። እንደ ትምህርት ፖሊሲ የቤተ ክርስቲያንን የአገልግሎት ቋንቋ የመበየን ሥልጣን የለውም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በቋንቋችን እንማር የሚለውን ጥያቄ ልናፍነው አንችልም” ያሉት ፈጽሞ ያለሥራቸው በመግባት የተደረገ ንግግር ነው። በዚህ ሳያቆሙ “በአማራ ክልል እና በትግራይ ክልል እንደሚደረገው በኦሮሚያ ክልልም በቋንቋቸው ሊማሩ ይገባል” በማለት ተናግረዋል። ይህ ፈጽሞ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ውጊያ ላይ መሆናቸውን ከሚያስረዳ በስተቀር የሚሰጠው ትርጉም የለም። በአማራ ክልል ምእመናን በአማርኛ መማራቸው እውነት ቢሆንም በትግራይ ክልል በትግርኛ ትምህርት እንደሚሰጥ የተናገሩት ግን ያለማስረጃ ነው። የትና መቼ ቢባሉ መመለስ የሚችሉት አይደለም። በአገራችን ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ቋንቋ ሆኖ ያገለገለውና እያገለገለ ያለው ግእዝ ቋንቋ ነው። አሁንም በሁሉም አካባቢዎች ቅዳሴ የሚቀደሰው በግእዝ ነው፤ ማሕሌት የሚቆመው በግእዝ ነው። እየተባለ ያለው ነገር እውነት ነው ቢባል እንኳን መምህራኑ ሳባክያነ ወንጌል እንጂ ጳጳሳት አይደሉም። በቋንቋ ማስተማርን መፍታት የሚቻለው ሰባክያንን በማብቃት እንጂ ሕገወጥ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት በመፈጸም አይደለም። በቋንቋ ማስተማርና ሕገወጦቹ ቡድኖች የፈጸሙት ሕገ ወጥ ሢመተ ጵጵስናም ፈጽሞ ግንኙነት የለውም። ሁለቱም ጋ እውነት አለ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት የሕገወጦቹ እውነት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ይህ አገላለጽ የተፈጸመውን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናዊ ጥሰት በቋንቋ እናስተምር ብለው የጠየቁ አካላት በቋንቋ አታስተምሩም ተብለው የተከለከሉ በማስመሰል የቀረበ ስለሆነ ፈጽሞ አግባብነት የሌለው ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ብቻ ሳይሆኑ ያላመኑበትንም ለማሳመን በተለያዩ በሀገረ ውስጥና በውጭ ዓለማት ሳይቀር አገልግሎቷን በቋንቋ ተደራሽ ለማድረግ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ጭምር በመደንገግ እየሠራችበት የምትገኝ መሆኗ እየታወቀ የሕገ ወጡን ቡድኑን ፍቅረ ሢመተ ጵጵስና በቋንቋ ከመገልገል ጋር በማዳበል የቀረበው ስሑት ግላጼ ሊታረቅ የሚገባው ነው። በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በቋንቋ የማስተማር ዓላማው ነፍሳትን በሚረዱት ቋንቋ ከእግዚአሔር ጋር ለማገናኘትና ለመንግሥተ ሰማያት የበቁ ለማድረግ እንጂ ቋንቋን ማሳደግ አይደለም። የቋንቋ ልማት የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑን ከዘነጉት ልናሳስብዎ እንወዳለን። ቤተ ክርስቲያን ግን በየትኛውም ክልል ቢኖሩ ቋንቋውን መስማት እስከቻሉ ድረስ በአንድ ቋንቋ ከማስተማር የሚከለክላት ነገር የለም። ቋንቋውን እስካልሰሙ ድረስ ደግሞ በሚሰሙት ቋንቋ ማስተማር ከአምላኳ የተረከበችው መንፈሳዊ ኃላፊነቷ ነው። መንግሥት በሚሰሙት ቋንቋ ካልሰበካችሁ ብሎ “በብሔር ተዋጽዖ” የራሱን ጳጳሳት የሚሾምበት አግባብ ሊኖር አይገባም። በዚህ ረገድ ክፍተቶች መኖራቸው ቢታመንም ዘውግን መሠረት በማድረግ የተፈጸመ አድሎ እንዳለ በማስመሰል የቀረበው ግን ፈጽሞ እውነትነት የለውም። “ሌላው ክልል እንደሚደረገው እኛም ክልል ያሉ ኦርቶዶክሳውያን የግድ በራሳቸው ቋንቋ መማር አለባቸው” የሚለው መመሪያ አዘል ማብራሪያም ኩሸትና ጣልቃገብነት መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን።
ቤተ ክርስቲያን ሁሉም በሚሰማው ቋንቋ ለማስተማር የራሷን መርሐ ግብር ዘርግታና ስልት ነድፋ እየሠራች ነው። ሕገወጥ ሢመት የፈጸሙትም ሆኑ በሕገወጥ መንገድ ተሹመናል የሚሉት አካላትም በተለያዩ ቋንቋዎች ማስተማር የሚችሉ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት የደከመችባቸውና ከዚህ መዓርግ ያደረሰቻቸው እንጂ በተአምር የተገኙ አይደሉም። ደግሞስ እነ አራርሳ ጎንፋ ከመቼ ወዲህ ነው ለኦሮሞ ሕዝብ በቋንቋው መማር የሚገዳቸው የሆኑት? አሜሪካ ለትምህርት ብለው ወጥተው ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ነገሌ ቦረና ሀገረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ በቅዱስ ሲኖዶስ ከአምስት ጊዜ በላይ ጥሪ ሲደረግላቸው አልመጣም ብለው በእምቢተኝነት የቀሩ አይደሉምን? ታዲያ ዛሬ በምን ምክንያት ነው በቋንቋ መማርን እንደተከለከሉ በማስመሰል በእርስዎ በኩል ለመናገር የፈለጉት? ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጉዛኑን ድርጊት ሕጋዊነት ያለው በማስመሰል ለማጽደቅና ለቡድኑ ዕውቅና ለመስጠት የሔዱበት ርቀት በእጅጉ የሚደንቅ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለተፈጸመው ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ጥሰት የወሰነችውን ሲኖዶሳዊ ውሳኔ ቋንቋን መሠረት በማድረግ የተወሰነ አድሏዊ ውሳኔ በማስመሰል የቀረበው አገላለጽ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክልና ዓላማዋን የረሳ ነው፡፡
ማንም ጣልቃ እንዳይገባ በማለት የዛቱት ሕገወጦችንም በመደገፍ አንጻር ከሆነ እባክዎ እርስዎም እጅዎትን ይሰብስቡልን። ንግግርዎ የመሪነት ጥበብ እንደጎደለዎት፣ አማካሪም እንደሌለዎት የሚያረጋግጥ ነው። እርስዎ ወይም አማካሪዎችዎ ስለ ቤተ ክርስቲያን ያላችሁ ግንዛቤ የተሳሳተ እንደሆነ ከንግግርዎ መረዳት ይቻላል። ቤተ ክህነትን ከቤተ ክርስቲያን የለዩ እንኳን አይመስልም። ቤተ ክርስቲያን ራሷ ክርስቶስ የሆነላት በምድር ያሉ የክርስቲያኖች በሰማይ ያሉ የቅዱሳን ኅብረትና አንድነት ናት። እየተዋጉ ያሉት ምድራዊ ተቋም ጋር ሳይሆን ከእነዚህ አካላት ጋር ነው። እናም እፍ ሲባል እንደሚበራ፣ ትፍ ሲባል እንደሚጠፋ እሳት መሆንዎን ረስተው በዚህ ልክ ቤተ ክርስቲያንን ለመገዳደር መነሣትዎ በእውነቱ መከራን እንጂ ዕድሜን አያረዝምም። ለማንኛውም ከፎከረ ቀርቶ ከወረወረ የሚያድን አምላክ እንዳለን በመተማመን ተጋድሏችንን እንደጀመርን ስናበሥርዎ በፍጹም ደስታ ነው፡፡ ምናልባት ባንክና ታንክ በእጅዎ ስላለ ለጊዜው በሥጋ ሊያስገድሉን ይችላሉ። ነገር ግን ሞት ከምትታየዋ ቤተ ክርስቲያን ወደማትታየዋ ቤተ ክርስቲያን የሚደረግ ጉዞ እንጂ የሕይወት መጨረሻ እዳልሆነ ስለምናምን ሞትን ልንፈራው አንችልም። አሸናፊውንም በቅርቡ የምናየው ይሆናል።
እስከዚያው በድጋሚ፡-
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈው ውሳኔ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከእርስዎ ጀምሮ በመሸኛ ደብዳቤ በአድራሻ የተላከ ስለሆነ በውሳኔው መሠረት ሰላምና ጸጥታ የማስከበር ኃላፊነትዎን በአግባቡ እንዲወጡ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
- ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ጥሰት በመፈጸም በሕገ ወጥ ሢመተ ጵጵስና ላይ የተሳተፉ አካላት በቤተ ክርስቲያን የተወገዙና ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ በመሆናቸው በተለያዩ አኅጉረ ስብከት እየፈጸሙት ያሉት ሕገወጥ ወረራና ሁከት እንዲቆም በድጋሚ እንጠይቃለን፡፡
- ቤተ ክርስቲያን የወሰነችውን ሲኖዶሳዊ ውሳኔ በዘር፣ በቋንቋና በፖለቲካ ምዛሬ በመተርጎም በእርስዎ ዘንድ የተያዘው አቋም ስሑት መሆኑን እየገለጽን በድርድርና በእርቅ የሚፈታ ቀላል ጉዳይ ተደርጎ መወሰዱ የቤተ ክርስቲያንን ቀኖናዊ ሥርዓት ካለመረዳት የመነጨ ብቻ ሳይሆን በውስጥ ጉዳይዋም ጣልቃ እንደመግባት ስለሚቆጠር ከዚህ አካሔድዎ እንዲታቀቡ እናሳውቃለን፡፡
- በሕገወጥ መንገድ ሢመተ ጵጵስና የሾሙና የተሾሙ አካላትን ቤተ ክርስቲያን የምትቀበልበት የራሷ ሃማኖታዊና ቀኖናዊ ሥርዓት ያላት በመሆኑ እና ይህንም ባስተላለፈቸው ውሳኔ በግልጽ ያስቀመጠች በመሆኑ በድርጊታቸው ተጸጽተው በንስሐ ሲመለሱ ብቻ የምትቀበላቸው ከሚሆን በስተቀር በፖለቲካዊ ጫና ሊፈጸም የሚችል ድርድር እንደሌለ ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡
ይቆየን!
No comments:
Post a Comment