Monday, February 20, 2023

በሲሞን መንገድ ላይ ተገኙት “አባ” ወ/ኢየሱስ ኢፋ (ፍቅሩ ኢፋ) - ክፍል አንድ

 


በህገ ወጥ መንገድ ከተሾሙት የጨረቃ ጳጳሳት ውስጥ አንዱ የቀድሞው አባ ወ/ኢየሱስ ኢፋ የአሁኑ ፍቅሩ ኢፋ ናቸው። እኚህ የቀደሞው አባት የአሁኑ አቶ ፍቅሩ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን የጀመሩት በቂልጡ ካራ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም ነው። ቂልጡ ካራ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም በምዕራብ ወለጋ ዞን የምትኝ የወረዳ ከተማ ስትሆን ገዳሟ የተመሠረተው በተዐምር ነው። እግዚአብሔር የለም የሚለው የደርግ መንግስት ተወግዶ ኢሀዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር አብዛኞቹ ወጣቶች ወደ ቤተክርስቲያን የተመለሱበት ጊዜ ነበር። ከዚህም ሌላ መናፍቃኑ በመንግስት ለውጥ ጊዜ የሚፈጠሩ ግርግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም “ኦርቶዶክስ ትክክል አይደለችም” ብለው በድፍረት ይሰብኩና በጎችን ከመንጋው ለይተው ያስኮበልሉ ስለነበረ፤ በሃይማኖታቸው ፍቅር የሚቃጠሉ ወጣቶች በተቃራኒው መልስ ለመስጠት እና አጽራረ ቤተክርስቲያንን እንዲያስታግስ ሱባኤ መያዝ ጀመሩ።

እነዚህ ወጣቶች ቅዱስ ዳዊት “የቤትህ ቅናት በልታኛለች” እንዳለው ለሃይማኖታቸው ካላቸው ቅንአት የተነሳ የሚያደርጉት እንጂ የሃይማኖት ትምህርት እውቀት ኖሯቸው አልነበረም። ከዚህም የተነሳ ይመስላል አንዳንዶችን ርኩስ መንፈስ የብርሃን መልዐክ መስሎ ይታያቸው የነበረው። በቂልጡ ካራ የነበረው ክስተት ግን እጅግ በጣም የተለየ እንደነበረ በቦታው የነበሩ ወንድሞች እንዲህ ይተርካሉ፡-
አንዲት እህት ነበረች። ይህች እህት ፊደል ስላልቆጠረች መጻፍም ሆነ ማንበብ አትችልም። ቢሆንም በሃይማኖት ጠንካራ ከሚባሉ እና በመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ከሚታወቁት እህቶች አንዷ ነበረች። ከእለታት በአንድ ቀን መልዐኩ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጾልኛል፣መጻፍና ማንበብም ችያለኹ ትልና እነ ኦርዶፋን ታስገርማቸዋለች። እነ ኦርዶፋም በድፈረቷ ተገርመው መጽሐፍ ሰጥተው አንብቢ ቢሏት ተቀብላቸው አንበለበለችው። ይባስ ብላም እሷ ከመጽሐፍ ቅዱሱ ጀርባ ሆና መጽሐፉን እንዲገልጡ ታዛቸውና የከፈቱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍና ቁጥር ነግራ ቃሉን በትክክል ታነብላቸው ያዘች።
በዚህ እጅግ በጣም የተገረሙት እነ ኦርዶፋ በማመን እና ባለማመን መካከል ሆነው ሲወዛገቡ አውቃ ካላመናችሁ ምልክት ልስጣችኹ በማለት የአሁኑ ቄስ የያኔው ዲ/ን በዳሳ በወቅቱ መንዲ ነበር። እሷም “በዳሳ አሁን ያለው መንዲ ነው። የሚመጣውም በአቶ እከሌ መኪና ነው። የሚወርደውም/ቦታውን ጠቅሳ/ እዚህ ቦታ ላይ ነው። ከተጠራጠራችኹ ሔዳችኹ ቆማችኹ አረጋግጡ። በማለት ላከቻቸው። እነሱም በጀ ብለው ኼደው ሲያጣሩ ዲ/ን በጻሳ በተባለው መኪና፣በተባለው ሰዓት እና ቦታ ሲወርድ አዩት። እውነት ለመናገር ለአኹኑ መናፍቃን ሰይጣን እንዲች ያለች ተዐምር እንዲያሳዩ ቢፈቅድላቸው አያኖሩንም ነበር!! ከዚህም የተነሳ ወንድም ኦርዶፋ እና ጥቂት ሰዎች ብቻ ተጠራጥረው እግዚአብሔር ምስጢሩን እንዲገልጽላቸው ሱባኤ ሲይዙ፣ሌሎች ከዲያቆን እስከ ቄስ የምታሳያቸውን ተዐምራት እያዩ ተከተሏት። ይህ በጊዜው ምንም የሃይማኖት ትምህርት እወቀት ላልነበረው የትኛውም ሰው አንዳች መንፈስ ቢገልጽላት ነው እንጂ በስጋና ደም ጥበብ አይደለም ብሎ ቢያምን አይፈረድበትም። ሰይጣን ግን የብርሃን መልዐክ መስሎ መገለጹ፣መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀሱ በጌታም ጊዜ የነበረ ልማዱ መሆኑን የተገነዘቡት ሰይጣንነቱ በተገለጸ ጊዜ ነው።
ዝናዋም በመላዋ ቂልጡ ካራ ናኘ። አጫሽ፣ ቃሚ፣ ጠጪ የነበረው የቂልጡ ካራ ወጣት ተዓምር ለማየት ተንጋጋ። መሠረታቸው ተዐምር የሆነው መናፍቃንም በቂልጡካራ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን አዳራሽ የሚደረገውን ተዐምር ለማየት ተሰበሰቡ። እሷም በጴንጤኛ ሙድ “አንተ ሲጃራ አጫሽ ነህ፣አንተ ዝሙት ሰርተሀል ወዘተ እያለች ትክክለኛ ግብራቸውን መናገር ያዘች። ግልብጥ ብሎ የወጣውም ሕዝብ የስነምግባር ጉድለት ያለባቸውን ወጣቶች ስትገስጽ እና እነሱም አምነው ሲንበረከኩ በእውነትም መላኩ ተገልጾላት ነው ብለው በሙሉ ልብ አመኑ። ይህችም እህት በሰይጣን ማታለል የወደቀች መሆኗን ስላልተገነዘበች ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ንዳ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወህዶ ቤተክርስቲያን ተደርጎ በማያውቅ መልኩ ካህናት አባቶችን አስቀምጣ ቡራኬ መስጠትን ዋና ሥራዋ አደረገች። ስብከተ ወንጌሉንም የግሏ አደረገች። እንዲያውም ከዕለታት ባንድ ቀን ስትፀልይ ከመሬት ከፍ ብላ ተንሳፋ እንደነበር ሰምተናል። ሆኖም ግን አንድ አባት/መሪጌታ ናቸው ይባላል/ በድርጊቱ በጣም እያዘኑ ግን ከጉባኤው የማይለዩ እና ሁል ጊዜም ይጸልዩ ስለነበር እንደልማዷ ሕዝቡ አራሹን ግጥም ብሎ ከአፍ እሰከ ገደፉ ሞልቶ ባለበት መድረክ ይዛ እጸልያለኹ፣አስተምራለኹ፣ትንቢት እናገራለኹ ስትል ድንገት በሙሉ ቁመቷ መድረኩ ላይ ትዘረራለች። ትልቁን አዳራሽ ሞልቶ ይከታተል የነበረው ምዕመን ተደናገጠ። መምህሩም የእግዚአብሔር ቀን እንደደረሰ፣እውነታውም የሚገለጽበት ጊዜው መሆኑን ስለተገነዘቡ ወደ መድረኩ ወጥተው ነብይ ነኝ ትል የነበረው እህት ማጥመቅ ሲጀምሩ ያደረባት ጋኔን መጮህ ያዘ። ተንፈራግጦ ላይመለስ ምሎም ይኼዳል። ተዐምር ለማየት የመጣው መናፍቅ እና የስም ኦርቶዶክስ ሁላ በእውነተኛው የእግዚአብሔር ሥራ ተደሞ ክርስቲያን የነበሩት በእምነታቸው ፀኑ፣መናፍቃን ወደመንጋው ተመለሱ። ይህንን ታሪክ የዛሬውን አያርገውና! ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ወደ ምዕራብ ወለጋ ለሐዋርያዊ ጉዞ በወጣበት ጊዜ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ እንደዘገበው አስታውሳለኹ።
አሁን ለእነ ኦርዶፋ ሰፊ የሥራ በር ተከፍቶላቸዋል። የተመለሰውን አስተምሮ የማጽናት፣ንሰሐ ያልገባውን አስተምሮ ንሰሐ ገብቶ ስጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ማድረግ። እነሱም አልሰነፉም። ጊዜም አላባከኑም። በእግዚአብሔር ቸርነት ሴባኤያቸው ውጤት ስላመጣ በእግዚአብሔር ቤት እንዲተከሉ ረዳቸው። እነሆ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይወላውሉ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ርትዕት መሆኗን አምነው ባሉበት ጸንተው አገልግሎታቸውን ሳያስታጉሉ እየፈጸሙ ይገኛሉ።
በዚህ መንገድ የመጣውን ምዕመን በቋንቋው የሚያስተምረው፣ንሰሐ የሚሰጠው፣ቀድሶ የሚያቆርበው ካህንና መምህራንን ማፍራት አማራጭ የሌለው መፍትኼ መሆኑን በማኅበረ ቅዱሳን የነቀምቴ ንዑስ ማእከል፣አሶሳ ንዑስ ማእከል እና በግምቢ ወረዳ ማእከል/የነቀምቴ ረዳት ንዕስ ማእከል/ ያሉ ወንድም እህቶች ከኪሳቸው ገንዘብ በማዋጣት መምህር በመቅጠር የአብነት ትምህርት እንዲጀመር መሠረት ጣሉ። በዚህም እግዚአብሔር ይመስገን ብዙ ፍሬ ማፍራት ተችሏል።
በኋላም አገልግሎቱ እንዲሰፋ እና ቀጣይነቱም እንዲረጋገጥ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል ሙሉ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ተደረገ። ማኅበሩም በገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች ዋና ክፍል በኩል ፕሮጄክቶችን በመቅረጽ በጎ አድራጊ ምዕመናን በማስተባበር ከምዕራብ ወለጋ፣ምስራቅ ወለጋ፣ቤኔሻንጉል ጉምዝ እና ጋምቤላ ደቀ መዛሙርትን ተቀብሎ በማስተማር ሰፊ ሐዋርያዊ ተልዕኮውን ተወጥቷል። እየተወጣም ይገኛል።
እነ አባ ወ/ኢየሱስ ኢፋ ከፊደል ቆጠራ እስከ ደረሱበት የትምህርት ሰረጃ የተማሩት በዚሁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ነው። በገዳም ቆይታቸውም ንጽህናቸውን ጠብቀው፣በትምህርት እራሳቸውን አሳድገው እንደ ብጹዑ አቡነ ሔኖክ ለማዕረገ ጵጵስና እንዲደርሱ ልዩ እንክብካቤ ይደረግላቸው እንደነበረ ከምዕራብ ወለጋ ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል። ግና ምን ያደርጋል! “የት ይደርሳል የተባለ ባሕር ዛፍ ቀበሌ ቆረጠው።” እንደተባለ በሲሞን መንገድ ላይ ተገኙ። ይቆየን እንቀጥላለን።

No comments:

Post a Comment

በሲሞን መንገድ ላይ ተገኙት “አባ” ወ/ኢየሱስ ኢፋ (ፍቅሩ ኢፋ) - ክፍል ሁለት

  እኚህ ሰው የእግዚአብሔርን ጥሪ ተቀብለው መንፈሳዊ ትምህርታቸውን መጀመራቸው አያጠራጥርም። በዚህም የሕይወት ምርጫቸውንም ቅዱስ ጳውሎስ “እንደኔ ብትሆኑ እወዳለኹ” ያለውን ተከትለው በሙሉ ጊዜያቸው እግዚአብሔርን እያመሠ...